" ኮሌጆች ወደ ጠቅላላ ትምህርት ለመግባት ዝግጅት ላይ ናቸው " -
አስተያየት ሰጪ የዘርፉ ተዋናዮች ➡️
" አብዛኞቹ ኮሌጆች በራሳቸው መንገድ መክሰማቸው አይቀርም "አብዛኞቹ የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት መቀጠል ስላልቻሉ ትምህርት ቤት ከፍተው ለመስራት በዝግጅት ላይ መሆናቸውን ስማችን አይጠቀስ ያሉና በዘርፉ የተሰማሩ ተዋናዮች ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡
የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማቱ፣ አሁን ባለው ሁኔታ ተማሪዎች ስለማያገኙና መንግስት ያወጣውንም መመዘኛ ስለማያሟሉ፣ ከጥቂቶች በስተቀር አብዛኞቹ በዘርፉ አይቀጥሉም ሲሉ ነው ያስረዱት።
አንድ የዘርፉ ተዋናይ አስተያየት ሰጪ፣ የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማቱ ወደ ጠቅላላ ትምህርት ገብተው ከመዋዕለ ህፃናት እስከ 12ኛ ክፍል ባለው ዘርፍ ለማስተማር ዝግጅት እያደረጉ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
በሌላ የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋም የሚሰሩ ሁለተኛ አስተያየት ሰጪም እንደዚሁ፥ " ተቋማቱ ተማሪ የማግኘት ፈተና ስለገጠማቸውና መንግስት ያወጣውንም አዲስ መመዘኛ ለማሟላት ከባድ ስለሆነ ወደ ጠቅላላ ትምህርት ለመዞር እንቅስቃሴ እንዳለ መረጃው አለኝ " ብለዋል፡፡
አንደኛው ባለሙያ ስለዚህ ጉዳይ በዝርዝር ምን አሉ ?" የኢትዮጵያ ትምህርትና ስልጠና ባለስልጣን፣ መጀመሪያ 84 የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በአዲሱ መስፈርት መሰረት ዳግም ለመመዝገብ ፈቃደኛ ስላልሆኑ እንደሚዘጉ ገልፆ ነበር፡፡ ሌሎች 9 ተቋማትም በተመሳሳይ አካሔድ እርምጃ ይወሰድባቸዋል ሲል ነበር፡፡
በኋላ ላይ በመመሪያው መሰረት ዳግም ለመመዝገብ ያመለከቱት 287 ተቋማትም አንዳቸውም መስፈርቱን እንዳላሟሉ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በሚድያ ገልጿል።
እነሱ በአዲሱ መመሪያ መሰረት መስፈርቱን እንዲያሟሉ የ45 ቀን ጊዜ ተሰጣቸው። ሆኖም የተሰጠው መስፈርት የሚሟላ አይነት ስላልሆነ 45 ቀን አልፎ ወደ ሶስት ወር እየሔደ ነው አሁን፡፡
ከዛም ሁላችንንም ጠሩንና ሁላችሁም ተመሳሳይ ደረጃ ላይ ስለሆናችሁ ያሉዋችሁን ተማሪዎች አስጨርሱ አሉን፡፡ አሁን እኛ ያሉንን ተማሪዎች በ2018 አስጨርሰን እንዘጋለን፡፡ በመንግስት እስካሁን ምንም አይነት እርምጃም አልተወሰደም ቀጣዩን እርምጃ እየጠበቅን ነው፡፡
እዚህ ሀገር ከነበሩት የግል ኮሌጆች ከ90 ከመቶ በላይ የሚሆኑት የመጀመሪያ ዲግሪ ያስተምራሉ፡፡ አሁን አብዛኞቹ ተማሪዎች ስለማያገኙ በመጀመሪያ ዲግሪ እያስተማሩ አይደሉም፡፡
ከ12ኛ ክፍል 3 በመቶ ብቻ ማሳለፍ ሲጀመር የአብዛኞቹ የግል ኮሌጆች የመጀመሪያ ዲግሪ ፕሮግራም ቆሟል። የ12ኛ ክፍል ፈተናን እያለፉ ያሉት ተማሪዎች አይደለም ለግል ኮሌጆች ለመንግስት ዩኒቨርሲቲዎችም አይዳረሱም፡፡ የማስተርስ ፕሮግራም ጀምረው የነበሩ የግል ተቋማትም ይህን ፕሮግራም አጥፈዋል አብዛኞቹ፡፡
መንግስት አዲስ መመሪያ ስላወጣ ብቻም ሳይሆን ተማሪ ስለማያገኙ ከገበያው ይወጣሉ አሁን አብዛኞቹ ስራ አቁመዋል፡፡ በሒደት ደግሞ በራሳቸው ጊዜ ይከስማሉ፡፡
በተለይም የተቀመጠው አዲስ መስፈርት ይሟላ ከተባለ ወደ 90 ከመቶ የሚሆኑት ኮሌጆች እንደሚዘጉ ግልፅ ነው፡፡ ምናልባት በጣም ጥቂቶች የራሳቸው ህንፃ ያላቸውና የተደራጁ ተቋማት ይቀጥሉ ይሆናል፡፡
አብዛኞቹ ተቋማት ወደ ጠቅላላ የትምህርት ዘርፍ ለመግባት ዝግጅት ላይ ናቸው፡፡ አሁን ባለኝ መረጃና ግምት (የግል አስተያየት) ከ40 - 50 ከመቶ የሚሆኑት የግል ተቋማት ወደ ጠቅላላ ትምህርት ይገባሉ፡፡ ትምህርት ቤት ለመክፈት መስፈርቱና ቅድመ ዝግጅቱ ከበድ ስለሚል በ2018 ዓ.ም ሙሉ ዝግጅት አድርገው በ2019 ዓ.ም ስራ ለመጀመር እየተዘጋጁ ያሉ ተቋማት አውቃለሁ፡፡
ከመዋዕለ ህፃናት እስከ 12ኛ ክፍል ለማስተማር በዝግጅት ላይ ይገኛሉ፡፡ ለምሳሌ እኛ በአዲስ አበባም በክልልም ያለንን ኮሌጅ ዘግተን ትምህርት ቤት ለመክፈት እየተዘጋጀን ነው ያለነው " ብለዋል።
ሁለተኛው አስተያየት ሰጪ በዝርዝር ምን አሉ ?" የተማሪ እጥረትና አሁን የመጣው አዲስ መስፈርት የተወሰኑ ተቋማትን ያከስማል፡፡ አሁን በማስተርስ ዲግሪ ብቻ ሲያስተምሩ የነበሩ ተቋማት በተማሪ እጦት የተነሳ ይህን ፕሮግራም አጥፈዋል፡፡ ዳግም ምዝገባው ምክንያት ነው የሆነላቸው፡፡ ዳግም ተመዝግበው ምንድነው የሚያደርጉት ተማሪ ከሌለ፡፡ የመጀመሪያ ዲግሪ የሚያስተምሩትም ተማሪ እያገኙ አይደሉም፡፡
በአጠቃላይ ኢንዱስትሪው ተመቷል፡፡ በጣም ተጎድቷል፡፡ ለዚህ ነው የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ወደ ጠቅላላ ትምህርት ዘርፍ ለመዞር እየተዘጋጁ ያሉት፡፡ ከተቋማቱ እንዲህ አይነት ፍላጎት መኖሩን አውቃለሁ እሰማለሁ፡፡
ቀድሞ የተዘጋጀ የትምህርት ቁሳቁሶች ስላሉዋቸው ለእነሱ ዘርፉ አዋጭ ነው፡፡ ትምህርት ቤቶች የሚያስከፍሉት ክፍያ አንድ የዲግሪ ተማሪ በወር ከሚከፍለው ያነሰ አይደለም፡፡ ለአስተማሪዎች የሚያወጡት የደመወዝ መጠንም እንደ ኮሌጅ ከፍተኛ ላይሆን ይችላል፡፡
አዲሱን መስፈርት ለማሟላት ከባድ ነው
በአዲሱ መመሪያ ተመዘገቡ ከተባሉት 287 ተቋማት አንዱ የእኛ ነው፡፡ ሐላፊዎቹ መጥተው ጉብኝት ካደረጉ በኋላ፣ የጎደለንን ነገር ነግረውን፣ አሟልተን ሰነዱን አስገብተናል፣ እስካሁን ምላሻቸውን እየጠበቅን ነው ያለነው፡፡
በሐላፊዎቹ ያልተጎበኙም ይኖራሉ ብቁ ያልሆኑትን አንጎበኝም ብለዋል፡፡ ሆኖም አንድም ተቋም መስፈርቱን አላሟላም ሲል ሰምተናል ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ፡፡
አንድም ተቋም መስፈርቱን ካላሟላ ይህን ሁሉ ተቋም በአንዴ ይዘጋሉ ብዬ አላምንም፡፡ ቁሳቁሱን ማሟላት ትችላለህ፣ የሰው ሀይል ግን እነሱ በጠየቁት መሰረት ከዬትም ልናመጣ አንችልም፡፡ የሰው ሀይል ለማሟላት ደግሞ የገንዘብ አቅም ፈተና ሆኗል ከዬት ይመጣል፡፡ ያላቸውንም ሰራተኛ ይዘው ለመቀጠል የሚቸገሩ ተቋማት አሉ " ብለዋል።
በዚህ ጉዳይ ዙርያ፣ ከኢትዮጵያ ትምህርትና ስልጠና ባለስልጣን፣ አስተያየትና ምላሽ ካገኘን በቀጣይ ይዘን እንቀርባለን፡፡
ቲክቫህ ኢትዮጵያ
አዲስ አበባ
#TikvahEthiopiaFamilyAA
@tikvahethiopia