አቶ አቤ ሳኖ በኢትዮጵያ የፋይናንስ ፎረም
***
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ግንቦት 7 እና 8 ቀን 2017 ዓ.ም ባዘጋጀው የኢትዮጵያ የፋይናንስ ፎረም የተለያዩ የፓናል ውይይቶች ተካሂደው ነበር።
‘FINANACIAL INCLUSION AND DEPENING: PROGRESS SO FAR AND PRIORITIES AHEAD’ (‘የፋይናንስ አካታችነት እና ጥልቀት፤ አሁናዊ ሁኔታ እና ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች’ እንደማለት ነው) በሚል ርዕሰ ጉዳይ በተዘጋጀው የፓናል ውይይት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ አቤ ሳኖ ተሳታፊ ነበሩ።
አቶ አቤ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የፋይናንስ አካታችነትን ለማረጋገጥ እያደረገ ያለውን ጥረት በውይይቱ አንስተዋል።
አቶ አቤ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለረጅም ዓመታት ትኩረቱን ትልልቅ የመንግስት የልማት ፕሮጀክቶችን መደገፍ ላይ አድርጎ ከመቆየቱ ጋር ተያይዞ የግሉን ዘርፍ በተለይም ታችኛውን የህብረተሰብ ክፍል በሚጠበቅበት ደረጃ የፋይናንስ ተጠቃሚ ማድረግ አለመቻሉን ገልፀዋል።
አሁን ባንኩ ላይ እንደ ግዴታ ተጥሎ የነበረው ይህ አቅጣጫ በመነሳቱ የፋይናንስ ተደራሽነቱን ለማስፋት እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ መሆኑን አቶ አቤ ተናግረዋል።
ከሁለት ዓመት በፊት ባንኩ በግሉ ዘርፍ የነበረው የተሰጠ ብድር 72 ቢሊዮን ብር ገደማ መሆኑን የገለፁት አቶ አቤ፣ በአሁኑ ጌዜ ከአምስት እጥፍ በላይ በማደግ ከ400 ቢሊዮን ብር በላይ መድረሱን አመልክተዋል።
አቶ አቤ በዚህ ዓመት ብቻ ባንኩ ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በመተባበር ከ782 ሺ በላይ ለሚሆኑ ደንበኞች ከ8.8 ቢሊዮን ብር በላይ ዲጂታል የፋይናስ አቅርቦት ማድረጉን ገልፀዋል።
ባንኩ የራሱን የሲቢኢ ብር አገልግሎት በመጠቀም ዲጂታል የብድር አገልግሎት ለመስጠት ቅድመ ዝግጅቱን ማጠናቀቁን የገለፁት አቶ አቤ፣ በሙከራ ደረጃ በተሠራው ሥራ ከ24 ሺ በላይ ለሚደርሱ ተጠቃሚዎች፣ ከ2.3 ቢሊዮን ብር በላይ ዲጂታል ብድር መስጠቱን ገልፀዋል።
አቶ አቤ የፋይናንሻል ቴክኖሎጂን በመጠቀም በኦሮሚያ ክልል 1 ሚሊዮን ለሚጠጉ አርሶ አደሮች ለማዳበሪያ መግዣ ከ14 ቢሊዮን ብር በላይ ዲጂታል ብድር መሰጠቱን ገልፀው፣ ይሄንኑ አበረታች እንቅስቃሴ ወደሌሎች አካባቢዎች ለማስፋት እየተሠራ መሆኑንም አመልክተዋል።
ባንኩ ከ112 ቢሊዮን ብር በላይ ፋይናንስ 349 ሺ የኮንዶሚኒየም ብድር አገልግሎት መስጠቱንም ነው አቶ አቤ የገለፁት።
ከ10 ዓመታት በፊት በእምነታቸው ምክንያት ወደ ባንክ መምጣት ያልቻሉ ወገኖችን ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት በመጀመር የባንክ ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉ በፋይናንስ አካታችነት የተመዘገበ ትልቅ ውጤት መሆኑን አቶ አቤ አስረድተዋል።
አቶ አቤ በባንኩ ከ7 ነጥብ 1 ሚሊዮን በላይ ከሚሆኑ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት አስቀማጭ ደንበኞች ከ180 ቢሊዮን ብር በላይ ተቀማጭ መኖሩን ገልፀው፣ በዚሁ ዘርፍ ከ71 ቢሊዮን ብር በላይ የፋይናስ አገልግሎት መቅረቡንም አስረድተዋል።
አቶ አቤ ባንኩ የብድር ተደራሽነቱን ለሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ለማስፋት እንደሚሠራ ገልፀው፣ ይህንንም ከሌሎች አካላት ጋር በመጣመር ጭምር እንደሚተገብር አመልክተዋል።
ሙሉውን ውይይት የሚከተለውን ማስፈንጠሪያ በመጠቀም እንዲመለከቱ ጋብዘናል፡
https://youtu.be/HvSS60w5oF0