✔️መልስ፦ የእግዚአብሔር ጽድቅ የተባለ ሃይማኖት በጻድቁ ምግባር ይገለጣል ማለት ነው። ከእምነት ወደ እምነት በእርሱ ይገለጣል ማለት ጻድቁ ከክብር ወደ ክብር ያድጋል ማለት ነው። እምነቱ በጻድቁ ክብር ይገለጣል ማለት ነው።
▶️፳፩. "የማይጠፋውንም የእግዚአብሔር ክብር በሚጠፋ ሰውና በወፎች አራት እግር ባላቸውም በሚንቀሳቀሱትም መልክ መስለው ለወጡ" ይላል (ሮሜ 1፥23)። ቢያብራሩልን?
✔️መልስ፦ ይህ የሚያመለክተው ሰዎች እግዚአብሔርን ማምለክን ትተው የሰው ቅርፅና የወፍ ቅርጽ እንዲሁም የእንስሳት ቅርፅ ያላቸው ጣዖታትን እንዳመለኩ ነው።
▶️፳፪. “ስለዚህ እርስ በርሳቸው ሥጋቸውን ሊያዋርዱ እግዚአብሔር በልባቸው ፍትወት ወደ ርኵስነት አሳልፎ ሰጣቸው” ይላል (ሮሜ 1፥24)። ይህ እንዴት ይተረጎማል?
✔️መልስ፦ በነጻ ፈቃዳቸው ተነሳሥተው የሰዎች ኅሊናቸው ወደክፉ ቢያዘነብል እግዚአብሔር ረድኤት ይነሣቸዋል ማለት ነው። አሳልፎ መስጠት ያለው ረድኤት መንሣቱን ነው።
▶️፳፫. “እንግዲህ ሕግን በእምነት እንሽራለንን? አይደለም። ሕግን እናጸናለን እንጂ” ይላል (ሮሜ 3፥31)። ይህ ክፍል ስለ መገረዝ ሕግ ነው የሚያወራው? ስለ ግዝረት ሕግ የሚያወራው ከሆነ ሕግን እናጸናለን ሲል የግዝረት ሕግ አልተሻረም ማለት ነው?
✔️መልስ፦ ከዚህ ሕግ ያለው ኦሪትን ነው። ሕግን እናጸናለን ማለቱ ከኦሪት አሥርቱ ትእዛዛት መጽናታቸውን ያመለክታል። ግዝረት ግን በጥምቀት ተተክቷል። ሕግን እናጸናለን ሲል መሥዋዕቱን፣ ግዝረቱንና የመሳሰለውን ሳይሆን በዋናነት አሥሩን ትእዛዛት እናጸናለን ማለቱ ነው።
▶️፳፬. ሮሜ 1፥3-4 ላይ ይህም ወንጌል የሚለው የሮሜን መልእክት ብቻ የሚመለከት ነው ወይስ መጽሐፍ ቅዱስን በሙሉ?
✔️መልስ፦ ወንጌል ማለት የምሥራች ማለት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍትን ሁሉ ከአራቱ ወንጌል አያይዞ ወንጌል ይላቸዋል። የብሉይ ኪዳን መጻሕፍትን ከአምስቱ ኦሪት አያይዞ ኦሪት እንደሚላቸው ሁሉ።
▶️፳፭. ሮሜ. 1፥28 ላይ "ሰነፍ አእምሮን ሰጣቸው" የሚለው እንዴት ይተረጎማል?
✔️መልስ፦ እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ሰነፍ አእምሮን አይሰጥም። ነገር ግን ሰው ኃጢአት ሲሠራ ረድኤተ እግዚአብሔር ይለየዋል። ረድኤተ እግዚአብሔር ሲለየው ሰነፍ አእምሮን ገንዘብ ያደርጋልና ይህን ለመግለጽ ሰነፍ አእምሮን ሰጣቸው ይላል።
▶️፳፮. ሮሜ. 2፥11 ላይ "እግዚአብሔር ለሰው ፊት አያዳላምና" ይላል። አንዳንድ ሰዎች እግዚአብሔር ያዳላል ይላሉ። በሀብት፣ በጤና፣ በልጅ እና በመሳሰሉት ሰው ከሰው እያነጻጸሩ። እንዴት ይታያል?
✔️መልስ፦ እግዚአብሔር ፍትሓዊ አምላክ ነው። ስለዚህ ለሁሉ የሚሻለውንና የሚጠቀምበትን ይሰጠዋል። ሰዎች በፆታ፣ በመልክ፣ በሀብት፣ በልጅ ሊለያዩ ይችላሉ። ይህ የሆነው ግን እግዚአብሔር ባወቀ ሁሉም ሊጠቀሙበት እንጂ አንዱ ሊጎዳበት አንዱ ሊጠቀምበት አይደለም። አንዳንዶች በስንፍና የሚመጡም አሉ። የእግዚአብሔርን አሠራር በሰው ሚዛን ለክቶ ያዳላል ማለት አይገባም። እንዳላዳላና እንደማያዳላ አሁን ማወቅ ካልቻልን ስንሞት ወይም በዳግም ምጽአት እናውቀዋለን።
▶️፳፯. ሮሜ. 3፥4 ላይ "ሰውም ሁሉ ሐሰተኛ ነውና" ሲል እንዴት ይተረጎማል?
✔️መልስ፦ ከዚህ ሰውም ሁሉ ተብለው የተገለጹ አይሁዳውያን ናቸው። ሐሰተኛ ናቸው ማለቱ መሢሑ አልመጣም በማለታቸው ሐሰተኛ መሆናቸውን ለመግለጽ ነው።
© በትረ ማርያም አበባው
✝️የዩቲዩብ ቻናሌ:- We belong to Christ ንሕነ ዘክርስቶስ
https://youtube.com/@edenawizechristos?si=6V4y-73OM3LTzhAf ነው።
🌻የፌስቡክ ገጼ Betremariam Abebaw
https://www.facebook.com/profile.php?id=100075547015721 ነው።